የፕሬስ መግለጫ

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመጀመሪያው መንፈቀ-ዓመት 1.44 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እና የአገልግሎት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ አቀረበ

ኮርፖሬሽኑ በስድስት ወራቱ ከታክስ በፊት 176,927,843 ብር ገቢ አግኝቷል

 

ጥር 28 ቀን 2014 /ም - አዲስ አበባ- የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በያዝነው የ2014 በጀት ዓመት አጋማሽ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በድምሩ 1.45 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እና የአገልግሎት ለአገር ውስትና ለውጭ ገበያ አቅርቧል፡፡ ለአገር ውስት የቀረቡት ምርቶች በዋነኝነት ለገበያ ማረጋጊያ የሚውሉ እህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችና የግንባታ ግብዓቶች ሲሆኑ ለውጭ ገበያ  ከቀረቡት ምርቶች መካከል የተለያዩ እህሎች፣ ቡናና ፍራፍሬ ይገኙበታል፡፡

በተለይም ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የታየውን ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ግምት ውስጥ በክምችት ይዞት የቆየውን ምርት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማሰራጭት ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ ችግሩን ለማቃለል 391 ሺህ ኩንታል እህል፤ 149.52 ሺህ ኩንታል ለፍጆታ የሚውሉ የፋብሪካ ምርቶች እና 43.8 ሺህ ኩንታል ፍራፍሬና አትክልት ምርት ለተጠቃሚዎች አሠራጭቷል፡፡

ከአደጋ ስጋት ሥራ አመራር በብድር ወጪ በማድረግ 567 ሺህ ኩንታል ስንዴ ለዱቄት ፋብሪካዎች፣ ለሀገር መከላከያ እና ለፖሊስ እንደዚሁም ለሌሎች ተቋማት የተሠራጨ ሲሆን፤ ሁለተኛ ሩብ ዓመት ላይ የውጭ ሀገር ስንዴ ግዥ በመከናወኑ በቀጣይ የሚሠራጭ 1,018,226 ኩንታል ስንዴ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች ለሥርጭት ዝግጁ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም 2.35 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት እና 93.16 ሺህ ኩንታል ስኳር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የሽያጭ መደብሮችና የችርቻሮ ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ ማሰራጨት ተችሏል፡፡  

ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መስፋፋት በግብአትነት የሚውለውን የሲሚንቶ ምርት አስፈላጊውን አሠራር በመከተል እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለመንግሥት ተቋማት፣ ለአልሚዎችና ለግለሰቦች የተለየ አደረጃጀትና አሠራር በመዘርጋት 243.5 ሺህ ኩንታል በ6 ወራቱ አሠራጭቷል፡፡  

የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታትና የውጭ ገበያ ልማት ትስስርን በማጠናከር፣ ገቢን ለማሳደግ 6.9 ኩንታል የብርዕና አገዳ እህል፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህል፣ ፍራፍሬ እና ቡና በመላክ 2.05 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም ብር 93.4 ሚሊዮን ገቢ ተገኝቷል፡፡

በሌላም በኩል ኮርፖሬሽኑ በ6 ወራቱ በመደበኛ ግዥ ከሀገር ውስጥ 1.23 ቢሊዮን ዋጋ ያለው 472.81 ሺህ ኩንታል ግዢ ያከናወነ ሲሆን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ ብር 3.16 ቢሊዮን ዋጋ ያለው 1.45 ሚሊዮን ኩንታል ምርትና አገልግሎት መሸጥ ሽያጭ አከናውኗል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በስድስት ወራት በአጠቃላይ 176,927,843 ብር ያልተጣራ ትርፍ ያገኘ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከነበረው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር የ39.1 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

-- // --