Management_News2.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስራ አመራር የ2016 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ፡፡ በኮርፖሬሽኑ ስር የሚገኙ ዘርፎች፣ የዋና መ/ቤትና የኮርፖሬት ሎጀስቲክስና ቴክኒክ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የሩብ ዓመት እቅድ ክንውን በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሩብ ዓመቱ በአጠቃላይ ሊገዛው ያቀደው መሠረታዊ የምርት አቅርቦት መጠን ብር 1,442,305,115 ዋጋ ያለው 297,648 ኩንታል ሲሆን በዚህ ወቅት ብር 2,778,723,940 ዋጋ ያለው 498,031 ኩንታል በመግዛት የዕቅዱን በመጠን 167 በመቶ፤ በዋጋ ደግሞ 193 በመቶ ማከናወኑ በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ተመልክቷል፡፡

ሽያጭን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በሩብ ዓመቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ ብር 2,920,244,100 ዋጋ ያለው 543,820 ኩንታል መሠረታዊ ምርትና አገልግሎት ለማሰራጨት አቅዶ ብር 2,665,653,200 ዋጋ ያለው 483,427 ኩንታል ምርትና አገልግሎት በማሰራጨት ዕቅዱን በመጠን 89 በመቶ በዋጋ ደግሞ 91 በመቶ አከናውኗል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በመሩበት ወቅት በሩብ ዓመቱ በትንሽ ጥረት የታየው አፈጻጸም አበረታች እንደሆነ ገልጸው በቀሪዎቹ ዘጠኝ ወራት የበለጠ በመስራት የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቀጣይ ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለባቸው በማለት በዝርዝር ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል ግዢና ሽያጭን ሁልግዜ በሁሉም መደብር/ቅርንጫፍ መተግበር፣ ገቢን ማሳደግ፣ እያንዳንዱን ፈጻሚ በውጤት መመዘን፣ ወጪ ቆጣቢ ስልት መጠቀም፣ ነባሩን በማጠናከር አዳዲስ የምርት አቅርቦት ላይ መስራት፣ የፋይናንስ ሥራን ማጠናቀቅ (IFRS/ኦዲት)፣ ትልቅ ገቢ የሚያመጡ ስራዎች ላይ ማተኮር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሰራተኞች የፌዴራል ፖሊስ አባላት በተገኙበት ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ጥቅምት 5/ 2016 ዓ/ም ከረፋዱ 4፡30 በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ-ስርዓት በማካሄድና የኢትዮጵያን ብሄራዊ የህዝብ መዝሙር በመዘመር አከበሩ፡፡

የዘንድሮው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን "የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው" በሚል መሪ ቃል በሃገር አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ እቴነሽ ገ/ሚካኤል ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክተው ባደረጉት አጭር ገለጻ አገራችን ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዥ ወራሪዎች ድንበሯን ተከላክላ፤ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች የጥቁር ሀገሮች መመኪያ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡

አያይዘውም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ ሦስትን መነሻ በማድረግ የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 በየዓመቱ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንዲከበር መደንገጉንና በዚህም መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ/ም በዓሉ በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ ቀን እንዲከበር መወሰኑን ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

ተጨማሪ ምስሎችን እዚህ ይመልከቱ፡፡

ExcerciseBook800.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለተማሪዎች መማሪያ የሚውል ከሶስት ሚሊየን በላይ መማሪያ ደብተር ከውጭ ሃገር በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡

ለገበያ የቀረበው ደብተር ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ፣ በቀላሉ ውሃ የማያስገባ (water proof) ጠንካራ ሽፋን (double cover) ያለው ሲሆን ዋጋው ለአዲስ አበባ በችርቻሮ 48 ብር እና በጅምላ ደግሞ 50 ብር ሲሆን ለክልሎች መጠነኛ የትራንስፖርት ታሪፍ ተጨምሮ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡ ደብተሮቹን በኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ንግድ ስራ ዘርፍ መደብሮች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ ዘርፍ ማከፋፈያዎችና የእህልና ቡና ንግድ ስራ ዘርፍ ማእከላት ማግኘት ይችላል፡፡

GridArt_20231012_110101692.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ በተሟላ ሁኔታ ለመፈፀም ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ ላይ ይገኛል፡፡ ከምርት ግዥና ሽያጭ ጋር በተያያዘ ኮርፖሬሽኑ በነሐሴ ወር በሀገር ውስጥ እና በኤክስፖርት ገበያ ለመሸጥ ያቀደው የእህል፣ ቡና፣ የፍጆታ ዕቃ እና አትክልት እና ፍራፍሬ ምርት መጠን 89 ሺህ ኩንታል በብር 556.4 ሚሊዮን ሲሆን 164.8 ሺህ ኩንታል በብር 925.1 ሚሊዮን በመሸጥ ዕቅዱን በመጠን 185 በመቶ እንዲሁም በዋጋ 166 በመቶ አከናውኗል፡፡

 

በአጠቃላይ በነሐሴ ወር በሀገር ውስጥ 45.2 ሺህ ኩንታል እህል፣ ቡና፣ ሲሚንቶና የምግብ ዘይት በብር 217.8 ሚሊዮን ለመሸጥ ዕቅድ ተይዞ 123.9 ሺህ ኩንታል እህል፣ ቡና፤ ሲሚንቶና የምግብ ዘይት በብር 556.52 ሚሊዮን በመሸጥ በመጠን 276 በመቶ፤ በዋጋ 255 በመቶ ለማከናወን ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በወሩ ውስጥ 576 ኩንታል ቡና በብር 16,758,720 ኤክስፖርት በማድረግ ገቢ ተገኝቷል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በነሐሴ ወር ላይ ለመሸጥ ያቀደው የአትክልትና ፍራፍሬ እና የፍጆታ ምርቶች መጠን 26.8 ሺህ ኩንታል በብር 174.5 ሚሊዮን ሲሆን በዚህ ወቅት 16.4 ሺህ ኩንታል በብር 181.9 ሚሊዮን በመሸጥ የዕቅዱን በመጠን 61 በመቶ በዋጋ ደግሞ 104 በመቶ ማከናወን ችሏል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በነሐሴ ወር ላይ ለመሸጥ ያቀደው የፍጆታ ሸቀጦች መጠን 17.13 ሺህ ኩንታል በብር 164.7 ሚሊዮን ሲሆን በዚህ ወቅት 22.8 ሺህ ኩንታል በብር 169.9 ሚሊዮን በመሸጥ ዕቅዱን በመጠን 133 በመቶ በዋጋ ደግሞ 103 በመቶ አከናውኗል፡፡

DSC_0995_032358.JPG

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራስ ቴአትር ጋር በመተባበር የ2016 ዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሆስፒታሎች ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማንና ወላጅ እናቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ስጦታ የማበርከትና የመልካም አዲስ ዓመት ምኞት መግለጫዎችን የማስተላለፍ መርኃ ግብር አካሄደ፡፡

ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ/ም በተካሄደው በዚህ የእንኳን አደረሳችሁ ጉብኝትና የስጦታ መርኃ ግብር ኮርፖሬሽኑ በ160 ሺህ ብር ወጪ የተለያዩ የታሸጉ ምግቦች፣ ፍራፍሬና የንጽህና መጠበቂያዎች በማዘጋጀት በጥሩነሽ ቤጂንግ፣ በአበበች ጎበና፣ በምኒልክ፣ በዘውዲቱ፣ በራስ ደስታ፣ በየካቲት 12 እና በጋንዲ ሆስፒታሎች በመገኘት ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን፣ እናቶችና ህጻናት ከቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አበርክቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የማኅበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ዓለማየሁ በመርኃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ እየተገበረ ከሚገኛቸው የአገር ውስጥ ገበያን የማረጋጋት፣ ለአምራቹ ገበያን የመፍጠርና የኤክስፖርት ግኝትን የማሳደግ ተልዕኮዎች በተጓዳኝ በተለያዩ የማኅበራዊ ኃላፊነት ትግበራ ላይ በመሣተፍ የህብረተሰብ አጋርነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተ መምጣቱን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመትም ለየት ባለ መልኩ ከራስ ቴአትር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ሴቶችና ህጻናት ላይ በማተኮር ለ250 ህሙማን በሰው አምስት መቶ ብር የሚሆኑ የኮርፖሬሽኑን ምርቶች በመያዝ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የማስተላለፍ፣ ታማሚዎችን የማጽናናትና ድጋፍ የማድረግ ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ ይህን አቅመ ደካሞችን የመርዳት ተግባሩን እያጠናከረ እንደሚሄድ ቃል የገቡት ወ/ሮ ትዕግስት፤ በዚህ ረገድ መሰል ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” የሚለውን የሀገራችንን ብሂል ወደ ተግባር በመለወጥ በተለይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚታዩባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየትና አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡