የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገራችን ያለውን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለመቋቋም የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችን በማከፋፈል ገበያውን ማረጋጋት አንዱ አገራዊ ተልዕኮው ነው፡፡

ዘንድሮም ኮርፖሬሽኑ ከውጭ የገዛውን ለአገር ውስጥ የገበያ ማረጋጊያ የሚውል ስንዴ በዕቅድ ከተያዘው 8 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ የመጀመሪው ዙር አገር ውስጥ በማስገባት ወደ ተለያዩ ክልሎች በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡

በመጀመሪው ዙር አራት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በአዲስ አበባ እና ከክልሎች በድሬደዋ፣ በባህር ዳር߹ በሻሸመኔ እና በአዳማ በተዘጋጁ የማሰራጫ ማእከላት እየገባ ነው፡፡

የስንዴ ግዥው በ11 ቢሊየን ብር የተከናወነ ሲሆን ስርጭቱ በአገራችን በሁሉም ክልሎች የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠና ትስስር ሚኒስቴር በሚሰጠው የኮታ መጠን መሰረት በዋነኝነት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት፣ ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ ሠራዊት፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ዳቦ አምርተው ለኅበረተሰቡ ለሚያቀርቡ ድርጅቶችና ለሌሎችም አቅርቦቱ ለተፈቀደላቸው አካላት የሚሠራጭ ሲሆን የአቅርቦቱ መኖር የስንዴ ገበያ ዋጋ እንዳይንር አስተዋጽዖኦው የጎላ ነው፡፡