001a.JPG

 

001b.JPG

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በዓል እንዲሁም ዓለም አቀፍ የኤች አይቪ ኤድስ ቀንን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ/ም ጎተራ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ሁለገብ የስብሰባ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

"በሥነምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ!" እና "አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች በእኩልነት ማድረስ- ወረርሽኙን መግታት!!" በሚሉ መሪ ቃሎች በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ከ230 በላይ የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ ከኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር የተጋበዙ ባለሙያዎች የኤች አይቪ ኤድስ ምንነትና መከላከያ ዘዴዎች እንዲሁም ጾታዊ ጥቃቶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ሰጥተዋል፡፡

ባለሙያዎቹ ከዚህ ጋር አያይዘውም በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነት በቀዳሚነት ከተመዘገቡት የካንሰር ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ስለሆነው የጡት ካንሰርና የማህጸን በር የጤና እክሎች ገለጻ የሰጡ ሲሆን ካንሰር እድሜያቸው ከ30-49 ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶችን የሚያጠቁ በሽታዎች በመሆናቸው ክፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ሆኖም በሽታዎቹ ፈዋሽና ቀላል ህክምናዎች ስላላቸው በየትኛውም የጤና ማዕከል ምርመራ በማድረግ መከላከል እንደሚቻል ለተሳታፊዎቹ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ከፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የመጡ ባለሙያ የሙስና ምንነት፣የሙስና ዓይነቶች፣የሙስና መንስኤዎች፣ ሙስና የሚያስከትለው ጉዳቶችና የመከላከያ ስልቶች በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ከሰጡ በኃላ ሙስና የሰው ልጆችን ሰላም በማሳጣት፣ፍትህ በመጓደል፣የሀገርን ኢኮኖሚ በማድቀቅ፣ማህበራዊ ኪሳራ በማድረስ እና ዲሞክራሲ ሥርዓትን በማቀጨጭ በኩል ዋና ሚና የሚጫወት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የዕለቱን መርሃ ግብር አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ጤንነቱ የተጠበቀ አመራርና ሠራተኛ ለተቋሙ እድገት ያለው አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ኮርፖሬሽኑ የንግድ ተቋም ከመሆኑ አንጻር አገልግሎት አሰጣጡን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ ደንበኛ ተኮር በማድረግ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ለማስፈን ተከታታይ ስልጠናዎች እንደተሰጠ እና ወደፊትም እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

አያያዘውም የድርጅቱ ውጤታማነት የሚለካው በደንበኞቻችን እርካታ ብቻ በመሆኑ ሁሉም ሠራተኛ በድርጅቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር ተፈጽሞ ሲገኝ ለሚመለከተው የሥራ ክፍል ጥቆማ በመስጠት፣አገልግሎት ሲሰጥም የመልካም ሥነምግባር እሴቶች በመላበስ ማገልገል እንዳለበት አሳስበው በተለይ በፀረ-ሙስና ትግሉ ሁሉም ሠራተኛ ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡