የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አብረውት ከሚሰሩ ደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የምክክር መድረክ ሰኔ 15/ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል አካሄደ፡፡ በመድረኩ ላይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በገበያ ማረጋጊያ ስራዎች በትስስር የሚሰሩ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች፣ ከፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተወከሉ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ለኮርፖሬሽኑ ምርት እና አገልግሎት አቅራቢ የመንግስት እና የግል የንግድ ተቋማት ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ፣ የዱቄት ፋብሪካ ባለንብረቶች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ በቀረበው የውይይት የመነሻ ጽሁፍ በኮርፖሬሽኑ ንግድ ስራ ክፍሎች እና ኮርፖሬት ሎጅስቲክስ ዳሬክቶሬት በሚሰሩ የምርትና አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች እና በደንበኞችና መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚረዱ ሃሳቦች በኮርፖሬሽኑ የአሰራር ዘዴና አገልግሎት ማሻሻያ ዳ/ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ትእዛዙ ኃ/ጊዮርጊስ ቀርቧል፡፡
የመነሻ ጽሁፉን ተከትሎ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ከኮርፖሬሽኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

በውይይቱ ኮርፖሬሽኑ ለአርሶአደሩ እና ለሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ፍጆታ እቃዎች አምራቹ የገበያ እድል መፍጠሩ & ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት መንግስት በድጎማ ለገበያ ማረጋጊያ የሚያቀርባቸውን የምግብ ዘይት እና ስኳር የሀገር ውስጥና የውጭ ስንዴ በተመደበለት ኮታ መሰረት ለህብረተሰቡ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በማቅረብ ገበያን ለማረጋጋት ያደረገው ጥረት በተመሳሳይ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የተከሰተውን የሲሚንቶ ዋጋ ውድነት ለማረጋጋት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በመሸጥ አጋርነቱን ማሳየቱ የኮርፖሬሽኑ አመራር እና ሰራተኞች ለደንበኞች የሚሰጡት መስተንግዶ ጥሩ መሆኑ በጥንካሬነት ተገልጾል፡፡

እንደ ችግር ከተነሱት ጉዳዮች መካከል በስንዴ፣ የምግብ ዘይትና ስኳር የአቅርቦት መዘግየት መታየት፣ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት፣ የፍጆታ ምርቶች ግብይት ላይ አስገዳጅ ምርቶችን ውሰዱ መባል የሚሉትን ጉዳዮችን ኮርፖሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲፈለግ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱት አስተየየቶች የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ደንበኞቹና ባለድርሻ አካላት በሚጠብቁበት ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት እና ባቀደው ዕቅድ ልክ አፈጻጸሙን ለማሳካት በሀገር ውስጥ በሚፈለገው መጠንና ዋጋ የእህል ምርት ገበያው ላይ አለመገኘት፣ በመንግሥት ድጎማ ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ሀገር የሚገዛውና በኮርፖሬሽኑ የሚሰራጨው የውጭ ስንዴ ግዥ ጨረታ መስተጓጎል፣ ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ለሚገዙ የፍጆታ ሸቀጥ ምርቶችም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ፍላጎትና አቅርቦቱ አለመመጣጠን፣ ኮርፖሬሽኑ ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸው የቡና፣ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የገበያ ዋጋ መብለጥና የምርቶቹ ዋጋ መዋዠቅ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የመንግስት የልማት ድርጅት እንደመሆኑ ወጪውን ራሱ እንደሚሸፍንና የትርፍ ህዳጉ ግን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተመላከቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በውይይቱ ማጠቃለያ በመድረኩ የተሳተፉ አካላትን በማመስገን የተሰጡ አስተያየቶችን እንደ ግብአት ወስደን አገልግሎታችንን ይበልጥ ለማሻሻል እንጠቀምበታለን ብለዋል፡፡ መድረኩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም የላቀ አጋርነት ላሳዩ ደንበኞች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን 13 ደንበኞች የእውቅና የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት ከኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡