የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የደንበኞችና ባለድርሻ አካላት መድረክ ግንቦት 26 እና ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ/ም በሻሸመኔ እና አዳማ ከተሞች ተካሂዷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የአገልግሎት አሠጣጡን ለማሻሻል በትኩረት ከሚንቀሳቀስባቸው መስኮች አንዱ በሆነው በዚህ የደንበኞችና ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ የህብረት ሥራ ማኅበራት፣ የምርት አቅራቢዎችና አከፋፋዮች፣ የዞንና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኃላፊዎች፣ የንግድና ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የግል ባለኃብቶችና ከኮርፖሬሽኑ ጋር በልዩ ልዩ የግንኙነት መስኮች የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታው ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና የኮርፖሬሽኑ የሥራ ዘርፍ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ኮርፖሬሽኑ በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት የሸማቹንና ኅበረተሰብና የአምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሚሠራና በተለያዩ የምርት ማጓጓዣና ማደራጃ አውታሮች የተደራጀ መንግሥታዊ የልማት ተቋም መሆኑን አውስተው፤ በዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ ምርቶችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አቅርቦ በማረጋጋት ሠፊ ሥራዎች መሥራቱን በውይይት መድረኮቹ አስረድተዋል፡፡
በከፍተኛ መጠን ምርት አምርተው ህብረተሰቡ ዘንድ መድረስ ላልቻሉ አምራች የህብረተሰብ ክፍሎችም ምርታቸውን ካሉበት ድረስ በመረከብ ምርታቸው እንዲታወቅና እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ለኅበረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በየጊዜው ማሻሻል እንደሚገባ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ መድረኩ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ መስኮች እየከወናቸው የሚገኙ ተግባራትን በተመለከተ ግብዓቶችን በመቀመር ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና በአገሪቱም የብልጽግና ሂደት ውስጥ ተገቢውን ሚና ለመጫወት ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ተደራሽነቱን ለማሳደግ፣ በአሠራርና በአፈጻጸም የሚታዩ ክፍተቶች ካሉ ተወያየቶ በመፍታት በቅንጅታዊ አሠራር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እንደሚረዳ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
በመድረኮቹ የኮርፖሬሽኑን የሥራ ወቅታዊ አፈጻጸም የሚያሳይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ አጠቃላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቶቹ እንደ ስኳርና ዘይት ካሉ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶች የአቅርቦት መጠንና ኮታ፣ ሥርጭትና ኮታ፤ በምርቶች ዋጋ፤ በአገልግሎት አሠጣጥ፣ በምርት ግብይትና አቅርቦት ላይ እንቅፋት በሆኑ አሠራሮች፤ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በተለይም ኮርፖሬሽኑ በሚያካሂደው የገበያ ማረጋጋት ሥራ ውስጥ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫና እየፈጠሩ ባሉ የንግድ አካላት፣ አሠራሮችና ሰው ሠራሽ ችግሮች፤ በምርት ጥራት፣ በጸጥታ፣ በገበያ መረጃ ተደራሽነት፣ እንዲሁም ተጠናከረው መቀጠል በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችችን በመቀላቀልና የምርትና አገልግሎት መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት ያግኙ!
ድረገጽ፡- https://www.etbc-ethiopia.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/etbcofficial
ቴሌግራም፡- https://t.me/etbcinfo
ዜና ኢንሥኮ አንድሮይድ መተግበሪያ፡- https://t.ly/DiXR
ዩትዩብ ቻነል፡- https://www.youtube.com/@etbcinfocom4858
አስተያየትዎን በኢሜይል አድራሻችን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ያድርሱን፡፡