የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚያዚያ4-7/2011 ዓ/ም በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው 1ኛው አለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ፎረም እና የንግድ ትርዒት ባዛር ተሳትፎው በሁሉም ንግድ ሥራ ዘርፎች የሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶችን ለጎብኝዎች ማቅረብ ተችሏል፡፡ አንድ የንግድ ተቋምን ለማሳደግና በተሻለ ሁኔታ ቢዝነሱን ለማከናወን እንዲችል የገበያ ልማት ሥራ መሥራት በጣም ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለኮርፖሬሽኑ ጠቃሚ መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ 

ለሸማች ማህበራት፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለጅምላ አከፋፋዮች፣ ለቸርቻሪዎች፣ ለኢንቬስተሮችና ለውጭ ሃገር ተሳታፊዎች ኮርፖሬሽኑን ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በንግድ ትርዒቱ በኮርፖሬሽኑ በተዘጋጀው የቡና ጠጡ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጋበዝ ኮርፖሬሽኑ ስለተቋቋመበት አላማና በኮርፖሬሽኑ ስለሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶች ዝርዝር ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የተለያዩ የሚዲያ አካላት ስለኮርፖሬሽኑ ዝርዝር መረጃ በአካል ተገኝተው በመጎብኘትና ሰራተኞችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ የጎብኚዎችን ግብረ መልስ በተመለከተ በተለይ የፍጆታ እቃዎች ለምሳሌ ከውጪ የሚገቡ የዘይት ምርቶች በንግድ ትርዒቶች ላይ ለሽያጭ የሚቀርቡበት ዕድል ቢኖር፤ በፍጆታ እቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ የሚሠጠው አገልግሎት ለተቋማትና ቲን ቁጥር/ፈቃድ ላላቸው ብቻ የሚከናወን በመሆኑ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የማያደርግ ስለሆነ ይህ አሰራር ቢቀየር፤ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ በኩል የሚሸጡ ምርቶች የሚሸጡበት ዋጋ ዙሪያ ማስተካከያ ቢደረግ የሚሉ አስተያየቶችና ግብረ መልሶች ተወስደዋል፡፡