አዳዲስና ዘመናዊ አሰራር ለዘረጉ፣ የላቀና ተጨባጭ እድገት ላስመዘገቡ፣ መልካም ስማቸውን ጠብቀው ለአመታት በትጋት ለዘለቁ ተቋማት /MILESTONE, BRANDING AND REPUTATION/ አቢሲኒያ የጥራት ድርጅት እውቅና ለመስጠት ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ/ም በኢንተርሊግዠሪ ሆቴል (በቀድሞ ኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል) ባዘጋጀው የኢንደስትሪ ሽልማት መርሃ-ግብር ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ዘርፍ /ኢትፍሩት/ የከፍተኛ ክብር ሽልማት የወርቅ ዋንጫ፣ የወርቅ ሜዳሊያና የከፍተኛ ክብር ዲፕሎማ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ለዘርፉ ስራ አርዓያ የሆኑ አምስት ምርጥ ሰራተኞች የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ሲሸለሙ፣ የመካከለኛ ደረጃ ሁለት አመራሮች ደግሞ የኒሻን ተሸላሚ ሆነዋል፤ እንዲሁም የዘርፉ ስራ አስፈጻሚ የከፍተኛ ክብር (የኮርዶን) ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ይህ በሀገራችን በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተካሄደ የመጀመሪያው የሽልማት መርሀ ግብር ሲሆን ከ57ሺህ የኢንዱስትሪ ተቋማት የተመረጡት 50 ብቻ ሲሆኑ በአጠቃላይ ተቋማዊ ውጤታቸው ላይ ከ2009-2014 በተደረገ ውጫዊ ምዘና በ24 መሰረታዊ መለኪያዎች ላይ ተመስርቶ በተገኘ ውጤት እንዲመረጡና እንዲሸለሙ መደረጉን በሽልማት መርሃ -ግብሩ ወቅት ተገልጿል፡፡ ዘርፉ ይህንን ከፍተኛ ሽልማት ያገኘው በኮርፖሬሽኑ የስራ አመራር ቦርድ እና የኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት በሚሰጠው ስትራቴጂካዊ አመራር በመመራት፣ የዘርፉ ማናጅመንትና ሠራተኞች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ባደረጉት እገዛና ድጋፍ በመሆኑ ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ፤ ደስ አለን እያለ፣ ዘርፉ ይህንን ስኬት እንዲያስመዘግብ ድጋፍና እገዛ ላደረጉ የኮርፖሬሽኑ ቤተሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ትኩስና ጥራታቸውን የጠበቁ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይታወቃል፡፡
|
ኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአራቱም ዘርፎችና ከዋና መ/ቤት የተውጣጡ ሴት ሰራተኞች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በአንድነት ፓርክ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ/ም ጉብኝት አካሂደዋል፡፡ ጉብኝቱን ያዘጋጀውና ያስተባበረው የኮርፖሬት ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ትግስት አለማየሁ ከየዘርፉና ከዋና መ/ቤት የተወከሉ ሴት ሰራተኞች በጉብኝቱ መሳተፋቸውን ገልጸው በስራቸው የበለጠ ውጤታማ እና ጠንካራ እንዲሆኑ ለማገዝ በጽ/ቤቱ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በጉብኝት እያከበረ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በየዘርፉና በዋና መ/ቤት ያሉ ሴት ሰራተኞችን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ በጉብኝቱ የተሳተፉና ያነጋገርናቸው ሰራተኞች በአንድነት ፓርክ በመገኘት የሀገራቸውን ታሪክና የተፈጥሮ ሃብት በመመልከታቸውና በአጠቃላይ በጉብኝቱ መዘጋጀት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
|
ኮርፖሬሽኑ በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ለመሸጥ ካቀደው 2.29 ሚሊዮን ኩንታል የእህልና ቡና፣ የፍጆታ ዕቃ እና የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት 2.27 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ወይም የዕቅዱን 99 በመቶ ለገበያ አቀረበ፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ ለመሸጥ ያቀዳቸዉ ልዩ ልዩ ሸቀጦች መጠን 1.69 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን በዚህ ወቅት መሸጥ የተቻለው 2.05 ሚሊዮን ኩንታል ወይም የዕቅዱን 107 በመቶ እንደሆነ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ 1.23 ሚሊዮን ኩንታል እህልና ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና ፍጆታ ዕቃዎች ከሀገር ውስጥ አምራቾች ለመግዛት አቅዶ 944 ሺህ ኩንታል በመግዛት የዕቅዱን 77 በመቶ ማከናወን እንደተቻለ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የአቅርቦትና የግብይት ችግር የሚስተዋልባቸውና በአጭር ጊዜ የሚበላሹ የግብርና ምርቶች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 211 የመገበያያ ማዕከላት ምርቶችን ከአምራቹ በቀጥታ በመግዛት ለሸማቹ እያቀረበ ይገኛል፡፡ እስከ 900 ኪሎሜትር ርቀት በመጓዝ ከፍተኛ የግብርና ምርት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ለአምራቹ ተገቢውን ዋጋ ሰጥቶ በመግዛት የምርት እጥረት ወደ አለባቸው አካባቢዎች በማጓጓዝ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ይህም በመደረጉ አምራቾች በገበያ እጥረት ምክንያት ምርታቸው እንዳይበላሽና ባመረቱት ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ሸማቹ ህብረተሰብንም ከመደበኛ ገበያው የዋጋ ቅናሽ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
የማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችችን በመቀላቀልና ድረገጻችን በመጎብኘት የምርትና አገልግሎት መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት ያግኙ!
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/etbcofficial
ቴሌግራም፡- https://t.me/etbcinfo
ዜና ኢንሥኮ አንድሮይድ መተግበሪያ፡- https://t.ly/DiXR
ዩትዩብ ቻነል፡- https://www.youtube.com/@etbcinfocom4858
አስተያየትዎን በኢሜይል አድራሻችን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ያድርሱን፡፡
ኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገራችን ያለውን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለመቋቋም የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችን በማከፋፈል ገበያውን ማረጋጋት እና የሃገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታት ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ |
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ የሚያስችል ማቀዝቀዣ መጋዘንን ጨምሮ ሁለገብ ሕንጻ ለማስጀመር የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓት የካቲት 25/2015 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሺ ቶታል ነዳጅ ማደያ አጠገብ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ይዞታ ውስጥ አከናወነ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የሁለገብ ህንጻው ግንባታ ከ 1.24 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደሚሰራና የሕንጻው ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም በተለይም የማቀዝቀዣ ግንባታው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ሳይበላሹ፣ ጥራታቸውን እንደጠበቁ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚው ጋር እንዲደርሱ ለማድረግ እና አምራቹ ምርቱ ገበያ እንዲያገኝ ለማበረታታት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሀሰን ሙሁመድ በበኩላቸው የሚገነባው ህንጻ ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅም መሆኑን በመጠቆም የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን እለት ታሪካዊ ቀን ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ህንጻው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በትጋት እንዲሰሩ ጠይቀው የስራ አመራር ቦርዱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የሚገነባው ሕንጻ ሁለት መሰረት ያለው ባለ አስር ወለል ቅይጥ የአገልግሎት ህንጻ እና ዘመናዊ ባለማቀዝቀዣ መጋዘን የያዘ ሲሆን በተጨማሪም የገበያ ማዕከል፣ ላቦራቶሪዎች እና የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ያካተተ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተግበር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች አቅርቦትን በጥራት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ በስነ-ስርዓቱ ወቅት ተመላክቷል።