የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በኮርፖሬሽኑ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ በክልልና በአዲስ አበባ ከሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ጎተራ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ መጋቢት 8 ቀን 2014 በተካሄደው ውይይት ላይ የ2014 የመጀመሪያ 6 ወራት የሥራ አፈጸጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በወቅቱ በመተመዘገቡ አበረታች ክንውኖችና መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊከዋናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ በኦፕሬሽን ሥራዎች፣ ትርፋማነትን በሚያጎለብቱ አሠራሮች፣ በወጪ ቀቅነሳ፣ በቅንጅታዊ አቅም ግንባታ፣ በግንዛቤ ፈጠራና በሌሎችም አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ መከናውን ስለሚገባቸው ተግባራት አቅጣጫዎች ተቀምጠ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
በሌላም በኩል በ2013 ዓ/ም በዕቅድ አፈጻጸም እና በለውጥ ሥራዎች የላቀ አፈጻጸም ላከናወኑ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የዕውቅናና ሽልማት መርኃ ግብር መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ/ም በጎተራ የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ በመርኃ ግብሩ ላይ የኢንሥኮ ሥራ አመራር ቦርድ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር እና የኮርፖሬሽኑ አመራር አባላት የተገኙ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ አፈጻጸምና የለውጥ ሥራዎች የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ሠራተኞች፣ ቡድኖችና የንግድ ሥራ ዘርፍ የዕውቅና ሰርቲፊኬት ከገንዘብና ዓይነት ሽልማቶች ጋር ተበርክቶላቸዋል፡፡ የዕውቅናና ሽልማት መርኃ ግብሩ የላቀ አፈጻጸም ያላቸውን ፈጻሚዎች ለላቀ አፈጻጸም ለማነሳሳትና ሌሎችም የእነርሱን ፈለግ በመከተል የሥራ አፈጻጸማቸውን እንዲያጎለብቱ ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው ተሸላሚዎችና የሥነ ሥርዓቱ ተሣታፊዎች ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራር እና ሠራተኞች ታህሳስ 12 ቀን 2014 ዓ/ም በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ እና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተለያዩ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ መርኃ ግብር አካሄዱ፡፡
በኮርፖሬት የማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት አስተባባሪነት ከኮርፖሬሽኑ አመራር እና ሠራተኞች የተሰባሰቡት አልባሳት፣ የህጻናትና የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች፣ የልጆች ወተት እና የታሸጉ ምግቦች መሆናቸውን የገለጹት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት በጅጋ፤ ኮርፖሬሽኑ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ግንባር ድረስ በመሄድ ለማስረከብ በጥቅሉ የሶስት ሚሊየን ብር ድጋፍ በገንዘብና በዓይነት ማዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገራችን ያለውን መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን ለመቋቋም የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችን በማከፋፈል ገበያውን ማረጋጋት አንዱ አገራዊ ተልዕኮው ነው፡፡
ዘንድሮም ኮርፖሬሽኑ ከውጭ የገዛውን ለአገር ውስጥ የገበያ ማረጋጊያ የሚውል ስንዴ በዕቅድ ከተያዘው 8 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ የመጀመሪው ዙር አገር ውስጥ በማስገባት ወደ ተለያዩ ክልሎች በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡
በመጀመሪው ዙር አራት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በአዲስ አበባ እና ከክልሎች በድሬደዋ፣ በባህር ዳር߹ በሻሸመኔ እና በአዳማ በተዘጋጁ የማሰራጫ ማእከላት እየገባ ነው፡፡
የስንዴ ግዥው በ11 ቢሊየን ብር የተከናወነ ሲሆን ስርጭቱ በአገራችን በሁሉም ክልሎች የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠና ትስስር ሚኒስቴር በሚሰጠው የኮታ መጠን መሰረት በዋነኝነት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት፣ ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ ሠራዊት፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ዳቦ አምርተው ለኅበረተሰቡ ለሚያቀርቡ ድርጅቶችና ለሌሎችም አቅርቦቱ ለተፈቀደላቸው አካላት የሚሠራጭ ሲሆን የአቅርቦቱ መኖር የስንዴ ገበያ ዋጋ እንዳይንር አስተዋጽዖኦው የጎላ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በዓል እንዲሁም ዓለም አቀፍ የኤች አይቪ ኤድስ ቀንን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ/ም ጎተራ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ሁለገብ የስብሰባ አዳራሽ አክብረዋል፡፡
"በሥነምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ!" እና "አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎች በእኩልነት ማድረስ- ወረርሽኙን መግታት!!" በሚሉ መሪ ቃሎች በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ከ230 በላይ የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ ከኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር የተጋበዙ ባለሙያዎች የኤች አይቪ ኤድስ ምንነትና መከላከያ ዘዴዎች እንዲሁም ጾታዊ ጥቃቶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ሰጥተዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ከዚህ ጋር አያይዘውም በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነት በቀዳሚነት ከተመዘገቡት የካንሰር ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ስለሆነው የጡት ካንሰርና የማህጸን በር የጤና እክሎች ገለጻ የሰጡ ሲሆን ካንሰር እድሜያቸው ከ30-49 ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶችን የሚያጠቁ በሽታዎች በመሆናቸው ክፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ሆኖም በሽታዎቹ ፈዋሽና ቀላል ህክምናዎች ስላላቸው በየትኛውም የጤና ማዕከል ምርመራ በማድረግ መከላከል እንደሚቻል ለተሳታፊዎቹ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ከፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የመጡ ባለሙያ የሙስና ምንነት፣የሙስና ዓይነቶች፣የሙስና መንስኤዎች፣ ሙስና የሚያስከትለው ጉዳቶችና የመከላከያ ስልቶች በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ከሰጡ በኃላ ሙስና የሰው ልጆችን ሰላም በማሳጣት፣ፍትህ በመጓደል፣የሀገርን ኢኮኖሚ በማድቀቅ፣ማህበራዊ ኪሳራ በማድረስ እና ዲሞክራሲ ሥርዓትን በማቀጨጭ በኩል ዋና ሚና የሚጫወት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የዕለቱን መርሃ ግብር አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ጤንነቱ የተጠበቀ አመራርና ሠራተኛ ለተቋሙ እድገት ያለው አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ኮርፖሬሽኑ የንግድ ተቋም ከመሆኑ አንጻር አገልግሎት አሰጣጡን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ ደንበኛ ተኮር በማድረግ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ለማስፈን ተከታታይ ስልጠናዎች እንደተሰጠ እና ወደፊትም እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡
አያያዘውም የድርጅቱ ውጤታማነት የሚለካው በደንበኞቻችን እርካታ ብቻ በመሆኑ ሁሉም ሠራተኛ በድርጅቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር ተፈጽሞ ሲገኝ ለሚመለከተው የሥራ ክፍል ጥቆማ በመስጠት፣አገልግሎት ሲሰጥም የመልካም ሥነምግባር እሴቶች በመላበስ ማገልገል እንዳለበት አሳስበው በተለይ በፀረ-ሙስና ትግሉ ሁሉም ሠራተኛ ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚያካሂዳቸውን የንግድ ሥራዎች በተሻሻሉ የአሠራር ዘዴዎች በመደገፍና ዘመናዊ፣ ወጪ ቆጣቢና የተቀላጠፈ አሠራርን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ የተለያዩ ዕቅዶችንና የአሠራር ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቀደም ሲል በመመሪያ ላልተደገፉ የተለያዩ የተቋሙ አሠራሮች መመሪያዎችን በማዘጋጀትና የነበሩትንም በማሻሻል የአገልግሎት አሠጣጥንና የስትራቴጂያዊ ግቦችን ስኬታማነት ማረጋገጥ ይገኙበታል፡፡ በዚህም ረገድ በተዘጋጁ ረቂቅ መመሪያዎች ዙሪያ የኮርፖሬሽኑን የበላይ አመራርና የሥራ ኃላፊዎች ያሣተፈ ውይይት ነሀሴ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ውይይት ከተካሄደባቸው ረቂቅ መመሪዎች መካከል የዕውቅናና ሽልማት አሰጣጥ፣ የተሸከርካሪ ስምሪት እንዲሁም የሥልጠናና ትምህርት መመሪያዎች የሚገኙበት ሲሆን ከተሣታፊዎች ጋር በተካሄዱ ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን በመቀመር በቅርቡ ጸድቀው በኮርፖሬሽን ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረጉ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡